ኢትዮጵያ ያለምንም ሜዳሊያ የተመለስችበት የአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና..

21ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከ25 ዓመታት በኋላ ያለሜዳልያ ድል ያጠናቀቀችበት ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ተሳትፎዋን የጀመረችው እ.አ.አ. በ1985 ዓ.ም. በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው ሶስተኛው ውድድር ላይ ነው፡፡ በሻምፒዮናው ላይ እስከ ናንጂንግ 2025 ድረስ በነበራት አጠቃላይ ተሳትፎ በተመዘገቡ ውጤቶችም የምንግዜም የሜዳልያ ሰንጠረዡ ላይ በ35 ወርቅ፣ 17 ብር፣ እና 16 ነሐስ በድምሩ በ68 ሜዳልያዎች ከዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ እና ሩሲያ ቀጥላ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ ትገኛለች፡፡

በዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው የመጀመሪያ የሜዳልያ ድል በ1997 ዓ.ም. ፓሪስ ላይ ሀይሌ ገብረስላሴ በወንዶች 3000 ሜትር ያሸነፈው የወርቅ ሜዳልያ ነበር፡፡ በፓሪስ በ1997 በሀይሌ የተጀመረው የሜዳልያ ድል የማስመዝገብ ገድልም በ2001 ዓ.ም. በፖርቹጋል ሊዝበን ከተካሄደው 8ኛው ሻምፒዮና በስተቀር ሳይስተጓጎል ለረጅም ግዜ መቀጠል ችሏል፡፡ እንዲያውም በ2022 ዓ.ም. በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው ውድድር ላይ ኢትዮጵያ 4 የወርቅ፣ 3 የብር፣ እና ሁለት የነሐስ በድምሩ 9 ሜዳልያዎች በማሸነፍ በሜዳልያ ሰንጠረዡ ላይ የበላይ ሆና ለማጠናቀቅም በቅታ ነበር፡፡ ላለፉት ሶስት ቀናት በፖላንድ ቶሩን ተካሂዶ የተጠናቀቀው ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ25 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ያለሜዳልያ ድል የሚመለሱበት ሆኗል፡፡

በ21ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን እና ኬንያን ጨምሮ 18 የአፍሪካ ሀገራት አትሌቶቻቸውን ልከው የተወዳደሩ ሲሆን በስሉስ ዝላይ በሴቶች ሴኔጋል እንዲሁም በወንዶች አልጄሪያ ካስመዘገቡት የነሐስ ሜዳልያዎች ውጪ የተቀሩት ሀገራት ያለሜዳልያ ወደሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በፓሪስ ከተጀመረበት እ.አ.አ. 1985 ዓ.ም. አንስቶም የአፍሪካ ሀገራት በወንዶች እና በሴቶች 800ሜ.፣ 1500ሜ.፣ እና 3000ሜ. ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ሜዳልያ ድል ውድድሩን አጠናቀዋል፡፡

የ2024ቱ የአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮን እና በ800 ሜትር የኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ማምጣት የቻለችው ፅጌ ድጉማ ከቪዛ ጋር በተገናኘ ችግር ወደስፍራው ማቅናት አለመቻሏ ይታወቃል። በቪዛ ጉዳይ ወደቦታው ያላቀናቸው አትሌት እሷ ብቻ ሳትሆን ሳሮን በርሄ፣ ሀርገወይን ካላዩ እና ሞሲሳ ስዩምም ይገኙበታል።

ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በትራክ ውድድሮች ያላት የበላይነት ከጊዜ ወደጊዜ እየተነጠቀች ይገኛል። በአንፃሩም በሀገር አቋራጭ እና በታላላቅ ማራቶን ውድድሮች አትሌቷቿ ባለድል እየሆኑ ይገኛል።

ዋቢ: ብዙአየሁ ዋጋው እ
፣ የአለም አትሌቲክስ ድረ-ገፅ እንዲሁም Track & Field Gazette

✍️ ዮናታን አየለ

Leave a Reply

Your email address will not be published.