የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አድዋን ማሰብ ጀምሯል!
“የካቲት – የጥቁሮች የነፃነት ወር” በሚል የ2018 ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የየካቲት ወር ጨዋታዎች በአጠቃላይ በህሊና ፀሎት እና የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ መታሰቢያ ይደረግባቸዋል።
ወላይታ ዲቻ ከ መቻል እና ሀዲያ ሆሳእና ከ ባህርዳር ከነማ ጨዋታም በምስሉ ላይ በምትመለከቱት መልኩ ጀግኖችን በማሰብ ተጀምሯል።
ይሄ አይነት ጀግኖችን የማክበር መንገድ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በጥቅምት መጨረሻ እና በህዳር መጀመሪያ ቀናት አካባቢ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ በየውድድር ዘመኑ እንደምንመለከት ይታወቃል።
አንደኛውን የአለም ጦርነት ተከትሎ ብዙ እግር ኳስ ሰዎች( ተጫዋቾች፣ የስታፍ አባላት እንዳሁም ደጋፊዎች) ሰራዊቱን ተቀላቅለው ጦርነት ዘምተዋል፤ አብዛኞቹም በህይወት አልተመለሱም። ይህን አጋጣሚ ለማሰብም ህዳር ወር በመጣ ቁጥር ተጫዋቾች እንዲሁም ዳኞች ቀይ ትንሽዬ አበባ ቅርፅ ደረታቸው ላይ አድርገው ወደሜዳ ይገባሉ። ይህቺ ትንሽዬ ቀይ አበባ የተመረጠችውም ከጦርነቱ በኋላ ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች በተፈጥሮ በብዛት በቅለው የነበሩት አበቦች እነዚሁ አበቦች ስለነበሩ ጊዜውን በሚገባ ለማስታወስም ጭምር ነው።
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ደግሞ የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ይደረጋል፤የእንግሊዝ ሰራዊት አባላትም ሜዳ ላይ ይጋበዛሉ፤ አሰልጣኞች የአበባ ጉንጉን ይዘው ወደሜዳ ይገባሉ። በስታድየሙ የሚገኙ ስክሪኖችም እነሱን የሚዘክሩ ምስሎች ሲያሳዩ ይስተዋላል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ታዲያ የጀግኖች ወር የተባለውን የካቲት ወር በዚህ መልኩ እያሰበ የሚቀጥል ይሆናል።
