” ዋንጫው ከእጃችን እንዲወጣ መፍቀድ የለብንም”- ራይስ

የአርሰናሉ ተጫዋች ዴክላን ራይስ የዘ ሰን የአርሰናል ጉዳዮች ዘጋቢ ከሆነው ‘ Simon Collings’ ጋር ባደረገው ቆይታ    ” የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ስናሸንፍ የሚወረወሩብንን ትችቶች ሁሉ ተቋቁመን እና ዋንጫው እንደሚገባን አሳይተን መሆን ይኖርበታል። ከወልቭሱ ጨዋታ በኋላ ጠንከር ያለ ውይይት አድርገናል። በጥሩ ደረጃ ላይ ሆነን ሳለ እንደዚህ አይነት ውጤቶች መመዝገባቸው እኛንም ሆነ ደጋፊዎችን አንገት ማስደፋቱን እናውቃለን። በዚህ አመት ለራሳችን ያስቀመጥነው ስታንዳርድ ዋንጫውን እንድናጣ አይፈቅድልንም” ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ሀሙስ እለት አርቴታ ለተጫዋቾቹ እረፍት ከሰጠ በኋላ ትላንት ማለዳ የቡድን ስብሰባ እንደነበራቸውና በድጋሚ ተነሳስቶ ዋንጫውን ለማሸነፍ የሚደረገውን ጉዞ ለመቀጠል መጪው የሰሜን ለንደን ደርቢ ጨዋታ ወሳኝ እንደሆነ ገልጿል። ” ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ የሚችል ስብስብ እንዳለን እናምናለን” ያለው ራይስ በዚህ የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች 3 ጨዋታዎች ብቻ እንደተሸነፉ አስታውሶ ከ22 አመታት በኋላ የሊግ ዋንጫውን ካሳኩ ድሉ  ከፍተኛ ትርጉም እንደሚኖረው ገልጿል።

ከደጋፊዎች ጋር በተያያዘም ” ከየትኛውም ጊዜ በላይ ደጋፊዎቻችን በአሁኑ ሰአት ያስፈልጉናል። እስካሁን አንድ ላይ መጥተን እዚህ ከደረስን በኋላ  ግኑኝነታችን መሻከር የለበትም። ሁላችንም በተመሳሳይ ጎራ መፋለም ይኖርብናል” ሲል ተናግሯል።

አርሰናል በፕሪምየር ሊጉ ነገ ምሽት 1:30 ሲል ከጎረቤቱ ቶተንሀም ጋር የሚጫወት  ይሆናል። ጨዋታውም በቶተንሀም ሆትስፐርስ ስታድየም ይደረጋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.