አትሌት መሰረት ደፋር ለ16ሺህ ሴቶች 5ኪ.ሜ. ሩጫን በ35 ደቂቃ በታች የማጠናቀቅ ፈተና አቀረበች!

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚያዘጋጀው መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. ለሚካሄደውና 16,000 ሴቶች ለሚሳተፉበት የ2018 ሳፋሪኮም የሴቶች ቀዳሚ 5ኪ.ሜ. የሩጫ ውድድር ልምምድ ቀጥሏል። የሁለት ጊዜ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የውድድሩ አምባሳደር መሰረት ደፋር ሴቶች አስቀድመው እንዲለማመዱ እና እንዲሮጡ ለማበረታታት ዓመታዊውን የ’35 ደቂቃ በታች’ ፈተና ይፋ አድርጋለች። ተሳታፊዎች ይህንን ግብ እንዲያሳኩ በስፖርት የዳበረ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን እንዲለማመዱ ለመርዳት፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለ4 ተከታታይ ሳምንታት የሚቆይ የሥልጠና መርሃ ግብር በማከናወን ላይ ይገኛል። ስልጠናው በሙያዊ አሰልጣኞችና አሯሯጮች (pace-makers) የሚታገዝ ሲሆን፤ በመሰረት ደፋር የአራት ሳምንታት የልምምድ ምክሮች የታጀበ ነው።

እንደላለፉት ዓመታት ሁሉ የውድድሩ መነሻና መድረሻ በቅርቡ እድሳት በተደረገለት በጃን ሜዳ አካባቢ የሆነው ይህ ውድድር ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባለፈ የሴቶች ስኬት የሚዘከርበት፣ ስራቸው የሚነገርበት እና እውቅና የሚያገኙበት እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው የሚበረታቱበት ልዩ መድረክ ሆኖ ለ22 ዓመታት ቀጥሏል።

በዘንድሮም በ“ተምሳሌት ሴቶች” (Icons Women) መካከል የሩጫ ውድድር የሚካሄድ ሲሆን፤ የአሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት በስራቸው ለመረጡት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይሰጣል። በ23ኛው ዓመት ሩጫ ውድድር ላይ ከስምንት የተለያዩ ዘርፎች የተመረጡ ታዋቂ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ይሳተፋሉ። ዘርፎቹም፦ ከኪነጥበብ፣ ከበጎ አድራጎት፣ ከመምህራን፣ ከስራ አመራር፣ ከጤና ባለሙያዎች፣ ከስራ ፈጣሪዎች፣ ከህግ ባለሙያዎች እና ከማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የተውጣጡ ናቸው። በዚህም መሰረት፦ ሉላ ገዙ፣ እማሆይ ዜና ማርያም፣ ቤቴልሄም ደሴ ፣ መቅደስ ሙሉጌታ(መቅዲዬ) እና ቤቲ ጂ በውድድሩ ላይ በ“ተምሳሌት ሴቶች” ዘርፍ ከሚሳተፉ ባለሙያዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ለውድድሩ የተመዘገቡ ተሳታፊዎች ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2018 ከዓለም ሲኒማ ጋር ቲሸርታቸውን መውሰድ እንደሚችሉም ታውቋል። ውድድሩ በሳፋሪኮም፣ ኢምፓክት ዴ.ኬ.ቲ (DKT)፣ ዳሽን ባንክ፣ አክቲቭ (Aktive)፣ የአየርላንድ ኤምባሲ፣ ዩኒሴፍ (UNICEF)፣ ፋብ የውበት ሳሙና፣ ዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ ቤት፣ ኢ.ቲ.ቪ እና አፍሪካ ሆስፒታል አጋርነት ይዘጋጃል።

ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተላከልን ጋዜጣዊ መግለጫ

Leave a Reply

Your email address will not be published.