በአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ድል ለተቀናጀው የአትሌቲክስ ቡድን ሽልማት ተሰጠው
የእውቅናና ማበረታቻ ሽልማቱ ተከናወነ፣
ሌሊት 9:20 ላይ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሶ አቀባበል የተደረገለት የ44ኛው የአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ቡድናችን ከተሳታፊ የአለም ሃገራት መካከል በ2 ወርቅ፣ በ7 ብር፣ በ1 ነሃስ፣ በጠቅላላው 10 ሜዳልያዎችን ሰብስቦ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ሃገሩ በድል ተመልሷል።
ለዚህ የጀግኖች አትሌቶቻችን ቡድን በስካይ ላይት ሆቴል ከረፋዱ 4:00 ጀምሮ በተካሄደ የእውቅናና የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት መርኃ ግብር ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የኢአፌ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ ስመ-ጥርና ታዋቂ አትሌቶች፣ የክለብና የአትሌቲክስ ማህበራት አመራሮች፣ የአትሌቶች ተወካዮች፣ ስመ-ጥር አሰልጣኞች፣ የስፖርት ሚድያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ቡድኑ በአውስትራሊያ ቆይታው ወቅት ስለነበረው አጠቃላይ ጉዳይ የቡድኑ የቴክኒክ መሪ አቶ አስፋው ዳኜ፣ የቡድኑ መሪ ወ/ሮ ሳራ ሃሰን፣ እንዲሁም ክብርት ረ/ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና ኦፊሻል በየተራ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ቡድኑ ከመሄጃ እስከ መመለሻው ወቅት ያልተገመቱ ፈተናዎች ያጋጠሙት ቢሆንም ሁሉንም በድል እንደተወጣቸው ተናጋሪዎቹ በንግግራቸው አስታውሰዋል።
በሽልማቱ መሠረትም ፌዴሬሽኑ ለወርቅ 45,000.00፣ ለብር 30,000.00፣ ለነሃስ 15,000.00፣ ለዲፕሎማ 10,000.00 እና ለተሳትፎ 5,000.00 ብር ለእያንዳቸው ሸልሟል።
የኢት/አትሌ/ፌዴ/ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቀደም ብሎ በወሰነው ውሳኔ መሠረትም ለጀግናዋና ብርቅዬዋ የበርካታ ሪከርዶች ባለቤት ለሆነችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ ለነበራት ቆራጥ ተጋድሎ ልዩ ሽልማት አበርክቷል።
በመርኃ ግብሩ ላይም ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታን ጨምሮ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የቋንቋና ባህል ልማት ዘርፍ ሚ/ር ደኤታ ክብርት ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ፣ የሥነ ጥበብና ኪነጥበብ ልማት ዘርፍ ሚ/ር ደኤታዋ ክብርት ወ/ሮ ነፊሳ አልመሃዲ፣ ክብርት ወ/ሮ ፈሪሃ መሃመድ በባህልና ስፖ/ሚኒስቴር በሚ/ር ደኤታ ማእረግ የሚኒስትሩ አማካሪ፣ የልዩ ልዩ ተቋማት አመራሮች በክብር ታድመዋል።

ክቡር አምባሳደር መስፍን ባስተላለፉት መልእክትም አትሌቶቻችን የአገራችን የድል ተምሳሌቶች እና ኩራቶች ናችሁ፣ የዘንድሮው የአድዋ ድል በአል እና የአትሌቶቻችን የድል ወቅት መገጣጠሙ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው፣ በድላችሁ የሚ/ር መ/ቤቱና መላው ህዝባችን ደስተኞች ነን ብለዋል።
አያይዘውም ከፊት ለፊታችን ለሚጠብቁን አህጉራዊና አለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ቀድመን በመዘጋጀትና ያለፉትን ገምግሞ አቅጣጫ በማስቀመጥ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ ለቡድኑ አቀባበል የኬክ ቆረሳ መርኃ ግብር አከናውኗል።
ቡድኑ ከአዲስ አበባ ተነስቶ እስከ ባትረስት ተጉዞ በተመለሰበት ሂደት የተለያዩ አሰራሮችን በማመቻቸትና በማሳለጥ ከፌዴሬሽኑ ጋር ሆነው የሰሩ ግለሰቦች፣ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ተቋማትን፣ እንዲሁም በካታር የኢትዮጵያ ኤምባሲንና አምባሳደር ፈይሰል አልይን ለቡድኑ ባደረጉት ደማቅ አቀባበል፣ መስተንግዶና አሸኛኘት ፌዴሬሽኑ ከልብ አመስግኗል።
ፌዴሬሽኑ ስፖንሰሮቹን:- የአዲዳስ ኩባንያንና ኦሮሚያ ባንክንም እንዲሁ አመስግኗል።
👉መረጃው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው
