በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አንጸባራቂ ድል የተጎናጸፈው ቡድን አቀባበል ተደርጎለታል ፡

በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ ከአለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ በሆነ አንጸባራቂ ድል ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል ፡

በዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ተካፍለው አስደሳች ውጤት ላስመዘገቡት የአትሌቲክስ ቡድን አባላት ነገ ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ/ም በአዲስ አበባ ደማቅ አቀባበል ይደረጋል።

የአትሌቲክስ ቡድኑ ከሚያርፍበት ስካይላይት ሆቴል ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ በአጀብ በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ስለሚጓዝ የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ይደረጋሉ።

ቡድኑ ከስካይ ላይት ሆቴል ተነስቶ በቦሌ ጎዳና ፣ መስቀል አደባባይ ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ-ክርስቲያን ፣ ሂልተን ሆቴል ፣ ፓርላማ ፣ አራት ኪሎ ፣ ራስ መኮንን ድልድይ ፣ ፒያሳ ፣ ቸርችል ጎዳና ፣ ቴዎድሮስ አደባባይ፣ ብሔራዊ ቴአትር ፣ ሜክሲኮ አደባባይ ፣ ለገሃር ፣ መስቀል አደባባይ በማድረግ መዳረሻውን ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ያደርጋል።

ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ሰዓት ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ የተከለከለ ሲሆን የአትሌትክስ ቡድኑ በአጀብ በሚያልፍበት ወቅት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳያጋጥም ከተፈቀደላቸው ተሽከርካሪዎች በስተቀር የተጠቀሱት መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ስለሚሆኑ ህዝቡ ይህን ተገንዝቦ የተለመደውን ትብብሩን እንዲያደርግ ተነግሯል ።
ወደ ቦሌ አየር መንገድ የሚመጡ መንገደኞችና ሌሎች ተጠቃሚዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ መገለጹን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

በአሜሪካ ኦሪገን በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ ከአለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ በሆነ አንጸባራቂ ድል ለተጎናጸፈው ቡድንና ለሀገራቸው ሜዳሊያ ገቢ ላደረጉ ጀግኖች ዳጎስ ያለ ሽልማት እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.