በዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያውያን ተከታትለው በመግባት አስገራሚ ድል ተጎናጸፉ።
ለ20ኛ ጊዚ በተደረግ የዱባይ ማራቶን በወንዶች ጌታነህ ሞላ የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል በአንደኝነት አጠናቋል፡፡
በአለም አቀፉ አትሌቲክሰ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠውና በተባበሩት አረብ ኤሜሬት ዱባይ ከተማ ስታንዳርድ ቻርተርድ ዱባይ ማራቶን ለ20ኛ ጊዜ አርብ ጥር 17/2011 ዓ.ም. ንጋት ላይ በተካሄደዉ የዱባይ ማራቶን ዉድድር ኢትዮጵያዉያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል፡፡
ጌታነህ ዉድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 2 ሰዓት ከ3 ዲቂቃ ከ34 ሰከንድ ሲሆን፥ በ26 ሰከንዶች የቦታውን ክብረወሰን ማሻሻልም ችሏል።
እንዲሁም አትሌት ሄርፓሳ ነጋሳ ከጌታነህ ሞላ በ14 ሰከንዶች ዘግይቶ በመግባት ዉድድሩን በሁለተኛነት ማጠናቀቅ ሲችል ሌላኛዉ ኢትዮጵያዊ አትሌት አሰፋ መንግስቱ ሦስተኛ በመውጣት የዱባይ ማራቶንን በበላይነት እንዲያጠናቅቁ አድርጓል።
እንዲሁም በሴቶች በተደረገ ውድድር ኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች ዉድድሩን 2 ሰዓት ከ17 ደቂቃ ከ8 ሰከንድ በመግባት ባለፈው ዓመት በሮዛ ደረጀ የተያዘውን የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል በአንደኝነት ስታጠናቅቅ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ ደበላ በሁለተኛነት እንዲሁም ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ ጉርሜሳ ሦስተኛነት በመዉጣት ዉድድሩን አጠናቀዋል፡፡
በዚህ መድረክ ከዚህ በፊት በተደረጉት ዉድድሮች በወንዶች 12 ጊዜ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሲያሸንፉ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ደግሞ ሶስት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሆኖ ተመዝግቧል እንዲሁም በሴቶቹ በተደረጉ ዉድድሮች 14ቱን ኢትዮጵውያኑ ሲያሸንፉ አትሌት አሰለፈች መርጊያም ለሶስት ጊዜያት በማሸነፍ በውድድሩ ስሟን በደማቅ መፃፍ የቻለች አትሌት ነች፡፡
የዘንድሮ የዱባይ ማራቶን ከዚህ ቀደም ከነበረው ዳጎስ ያለ ሽልማት መጠን በግማሽና ከግማሽ በታች የቀነሰ በመሆኑ አትሌቶቹ ላይ ቅሬታ አሳድሯል፡፡