ጆዜ ስሙን ያነሱለት ኡዜቢዮ ማነው?
ቪንሽየስ ጁንየር የዘረኝነት ጥቃት ተሰንዝሮብኛል ባለ ጊዜ ጆዜ ሞሪንዮ ” የዚህ ክለብ ሌጀንድ ኡዜቢዮ ጥቁር ነው። ቤኔፊካ ዘረኛ ክለብ አይደለም” የሚል አስተያየት ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል።
ዛሬ ደግሞ የባየርሙኒኩ አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ 12 ደቂቃ ያህል በቆየው ንግግሩ ላይ እንደኡዜቢዮ ያሉ ጥቁር ተጫዋቾች “በ1960ዎቹ አካባቢ ይደርስባቸው የነበረውን መከራ ጆዜ አያውቁም ወይ?” የሚል ሀሳብን ሰንዝሮ፤ ያኔም ቢሆን ኡዜቢዮ ከዘረኝነት ጥቃት እንዳላመለጠ ጠቅሷል። በእርግጥም ኮምፓኒ አልተሳሳተም።
ረቡዕ እለት በአራዳ ኤፍ 95.1 ኢትዮ-ማዕድ ሬድዮ ዝግጅታችን ላይ ስለኡዜቢዮ ያቀረብነውን ዝግጅት በፅሁፍ እንዲህ ልናስብባችሁ ወደድን።
ኡዜቢዮ ማነው?
የኡዜቢዮ ታሪክ በራሱ ጆዜ እንዳሉት የእኩልነት መለኪያ ሳይሆን ጥቁሮችን ምን ያህል የዘረኝነት ጥቃት እና ጭቆና እንደሚደርስባቸው ማሳያ ነው ይላል ‘The Game Theory’ በሚለው ዝግጅት ላይ የቀረበው ዘገባ..
የእግር ኳስን ታሪክ ጠንቅቀው ለሚረዱ ሰዎች ኡዜቢዮ የሚለው ስም አዲስ አይደለም። የሱ የእግር ኳስ መንገድ ከጎሎች እና ከዋንጫዎች በላይ ማንነት፣ ቅኝ ግዛት እና ፖለቲካ የሚንፀባርበቅበት ነው። ይሄ አመት ከኡዜቢዮ ጋር በተያያዘ በልዩነት እንድናነሳው ያደርገናሌ። ዘንድሮ ኡዜቢዮ የመጀመሪያው ባላንዶርን ያሸነፈ በቆዳ ቀለሙ ጥቁር የሆነ ተጫዋች ከሆነ 60 አመታትን የደፈነበት ከመሆኑም በተጨማሪ የትውልድ ሀገሩ አፍሪካዊቷ ሀገር ሞዛምቢክም ከፖርቹጋል ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች 50 አመታት የተቆጠሩበትም ጭምር ነው።
ኡዜቢዮ ሜዳ ላይ ለአመታት የተለየ ተሰጥኦውን እያሳየ የተጫወተ ሲሆን 733 ጎሎች አስቆጥሯል፤ 11 የሊግ ዋንጫዎች እና 1 የአውሮፓ ዋንጫ ደግሞ ከቤኔፊካ ጋር አሳክቷል። በብሄራዊ ቡድን ደግሞ ከፖርቹጋል ጋር የአውሮፓ ዋንጫን ከማሳካቱ በተጨማሪ በአለም ዋንጫም ሆነ በአውሮፓ ዋንጫ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ መሆን የቻለ የመጀመሪያው ተጫዋች ነው።በ1960ዎቹ ስሙ ሲገን ታዲያ ዝናው ፖለቲካዊ ምልክት ተደርጎም ይታይ ነበር።
ፖርቹጋል በዛን ሰአት በአንቶኒዮ ዴ ኦሊቨራ ሳላዛር አገዛዝ ስር የነበረች ሲሆን ይህ መንግስትም በአፍሪካ ሰፊ የቀኝ ግዛት መዳረሻዎች ነበሩት። የኡዜቢዮን ስኬትም እንደፕሮፖጋንዳ ተጠቅመውበታል። ፖርቹጋል ነጭ እና ጥቁርን በአግባቡ አስተሳስራ የምታኖር፣ በእኩል አይን የምታይ ሀገር እንድትባል የኡዜቢዮን ስኬት እንደማሳያ ይወስዱት ነበር።
Et, [2/21/2026 6:45 PM]
ኡዜቢዮ በ1942 ነበር ዛሬ ላይ ማፑቶ ተብላ በምትጠራው የሞዛምቢክ ዋና ከተማ የተወለደው። በፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ስርአት ስርም ለማደግ ተገዷል። ፖርቹጋል የሚገዟቸውን የአፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ‘ Indigenous Statue’ የተባለውን ህግ በመጠቀም ለሁለት ይከፍሏቸዋል። የመጀመሪያው ቡድን ‘ Civilized ‘ ሲሰኙ እነዚህ ህዝቦች ለፖርቹጋል የቅኝ ግዛት ፍላጎቶች የተገዙ እና በዚህም መሰረት ከፖርቹጋል ዜጎች እኩል ባይሆን እንኳን የተወሰኑ መብቶቻቸው የሚጠበቅብላቸው ናቸው። አንድ የቀኝ ግዛት ስር ያለ ሰውም ‘ Civilized’ ዘርፍ ውስጥ እንዲመደብ ባህላዊ ክንውኑን መተው አለበት፤የነሱን እምነት እና ባህልም ተቀብሎ ሊኖር ይገባል። ይሄን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ደግሞ ‘ Indeginous’ ሲሉ ይከፍሏቸው ነበር። እነዚህም ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ አይደረግም፣ ከፖለቲካዊ ተሳትፎ ይገለላሉ፣ ንብረት የማፍራት መብታቸው አይጠበቅላቸውም። ብዙ እድሎቻቸው ሆን ተብሎ ይዘጋባቸዋል።
አንዳንዴ ታዲያ የተለየ ተሰጥኦ ግን እነዚህን ህግጋት ሊያጥፍ ይችላል። የዚህ ማሳያ ኡዜቢዮ ነው። ኡዜቢዮ ገና ሞዛምቢክ ሳለ በሚያሳየው ተሰጥኦ የተነሳ ሌላኛው በቀኝ ግዛት የምትታወቀው ሀገረ ጣሊያን ክለቦቿ በተጫዋቹ ላይ ፍላጎት አሳይተው የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ ግን በቀጥታ ከትውልድ ሀገሩ ሞዛምቢክ ያመራው ወደቤኔፊካ ነበር። በ18 አመቱም ለቤኔፊካ ፈረመ። ከአመት አመትም ዝናው በአውሮፓ እግር ኳስ እየናኘ በመጣ ቁጥር የቆዳ ቀለሙ ጥቁር ከመሆኑ አንፃር የሳላዛር መንግስት ለነጮችም ሆነ ለጥቁሮች እኩል እድልን ያመቻቻል የሚለውን ምስል ለተቀረው አለም እንዲሰጥ አድርጓል።
በሞዛምቢክ ግን ታሪኩ ሌላ ነው፤ የቀኝ ገዢዎቹን ፍላጎት ባላከበሩት ላይ ምን ያህል ቀኝ ገዢዎቹ ኑሮን ያከብዱባቸው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። እንደ ኑኖ ዶሚንጎስ ያሉ የታሪክ ፀሀፍትም ኡዜቢዮ ለሳላዛር አገዛዝ የነበረውን ትልቅ ምስል ከማሳየት ወደኋላ አላሉም።
እንደኡዜቢዮ ያሉ ይሄንን ሰብረው መውጣት የቻሉ ተጫዋቾች ሌላኛው የሚያልፉበት ፈተና ደግሞ በነፃነት ስለመነሻቸው ባህል እና ማንነታቸው እንዳያወሩ ገደቦች መጣላቸው ነው። ኡዜቢዮም ምንም እንኳን በአፍሪካ ምድር ይወለድ እንጂ እውነተኛ ማንነቱን እንዲገልፅ የተወሰነ እድል ብቻ ነበር ያገኘው።
በተለያዩ የአፍሪካ ቅኝ ተገዢ ሀገራት የነፃነት እንቅስቃሴዎች ተጧጡፈው መቀጠላቸው እና የፖርቹጋል ወታደሮችም ወደቅኝ ተገዢ ሀገራት ሄደው በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ ማለፋቸው ቅሬታ እያስነሳ በማምጣቱ ከሳላዛር አንስቶ እስከ ማርሴሎ ካቴኖ የተገነባው አገዛዝ በወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ተደርጎበት እንዲወርድ ሲደረግ ቀኝ የተገዙት ሀገራትም ነፃ እንዲወጡ ሆነ። ያኔ ነበር ታዲያ ኡዜቢዮም ከ14 አመታት በኋላ ከቤኔፊካ ውጭ ወጥቶ ከፖርቹጋል ውጭ እንዲጫወት የተፈቀደለት።
ኡዜቢዮ አሁን ድረስ የፖርቹጋል እግር ኳስ ሲነሳ ስማቸው ቀድመው ከሚጠሩት ተጫዋቾች መሀል አንዱ ነው። ለአፍሪካ ደግሞ አፍሪካዊያን ምን ያህል ጫናዎችን ተቋቁመው ስኬት ላይ መድረስ እንደሚችሉ በማሳያነት ይጠቀሳል።
✍️ ዮናታን አየለ
