አዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ፣ አዲሱ የስፖርት አዋጅ እና የአትሌቲክሱ ጉባኤ

አዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ

ከሰሞኑ በስፖርቱ አበይት ሁነቶች የተከሰቱ ሲሆን በቅድሚያ ባሳለፍነው ቅዳሜ የነሀስ ደረጃ ተሰጥቶት በአዲስ አበባ ስታድየም የተካሄደው የግራንድ ፕሪ ውድድር በስፋት ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል። የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ ለስምንት ዓመታት ከውድድሮች ውጭ ከሆነ በኋላ አዲስ የመሮጫ ትራክ በተነጠፈለት ታሪካዊው የአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል። ይህ ውድድር የዓለም አትሌቲክስ የኮንቲኔንታል ቱር የነሀስ ደረጃ የተሰጠው ሲሆን  በመዲናዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄድ ዓለም አቀፍ የአንድ ቀን የአትሌቲክስ ውድድር በመሆኑ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ አዲስ ምእራፍ ተብሎለታል። በዚህ አለም አቀፍ ውድድር ላይ  ከተሳተፉ እውቅ አትሌቶች መሀከል አሜርካዊቷ የፓሪስ ኦሎምፒክ የ200 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ጋቢ ቶማስ ስትገኝ በ200 ሜትር እና በ100 ሜትር የበላይነት በመያዝ አጠናቃለች። በበርንጊሀሙ የ2022 የኮመን ዌልዝ ውድድር የወርቅ ሜዲሊያ ያሸነፈው የአፍሪካ ፈጣኑ ሰው የሚባልለት ፈርዲናንድ ኦማንያላም በውድድሩ ተሳትፎ 100 ሜትሩን 9:98 በመግባት አጠናቋል።



Credit: Tikvah Images

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓለም አትሌቲክስን ጥብቅ መስፈርቶች ለማሟላት የ”TimeTronics” እና ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የተጠቀመ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ለተሳታፊዎች እና ለልዑካን ቡድን አባላት ያለ ቪዛ (Visa-free) መግባት ተፈቅዶም ነበር። በኦቢኤን (OBN) ቀጥታ የተላለፈው ይህ ውድድር  ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሻምፒዮናን (በ2000 ዓ.ም) እና የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮናን (በ2007 ዓ.ም) ካስተናገደች በኋላ፣ ይህን ውድድር የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ለማረጋገጫነት እንደምትጠቀምበት ተገልፆ የነበረ ሲሆን እዛው ውድድሩ ላይ ከአለም አትሌቲክስ ሰዎች ኢትዮጵያ ለቀጣዩ አመት የወርቅ ደረጃ የ1 ቀን ውድድር ለማዘጋጀት ብቁ ነች ተብሎ መበሰሩ ይታወሳል። መንግስት ለዚህ ውድድር ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማድረጉ የተገለፀ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንዲሁም የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በስፍራው ተገኝተው ነበር። በውድድሩ ላይ ይገኛሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መከሀል የተወሰኑት አለመገኘታቸው በመስተዋሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እርምጃ እንደሚወስድ መግለፁም አይዘነጋም።

አዲሱ የስፖርት አዋጅ

በዚህ ሳምንት በእለተ ማክሰኞ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የስፖርት ልማት እና አስተዳደር አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል። ይህንን ተከትሎም የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ “አዋጅን በማዘጋጅት ህደት ውስጥ፣ ሀሳብ በመሰጠትና የበለጠ እንድዳብር በማድረግ የተሳተፋችሁ ሙሁራን፣የህግና የስፖርት ባለሙያዎች፣ጋዜጠኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሙሉ በራሴና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም ላቅ ያለ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ” ብለዋል። የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላትም የተለዩ ሲሆን የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንትም በአባልነት እንዲካተት ተወስኗል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጉባኤ እና ውሳኔዎቹ

በኢሊሊ ሆቴል ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 29ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተሻሻለ መተዳደሪያ ደንብ በማፅደቅ ጉባኤውን አጠናቋል። በፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ በዶ/ር አመንሲሳ ከበደ ቀርቦ የጉባኤው አባላት ሰፊ ውይይት ካደረጉበት በኋላ (በአንድ ድምፀ ተአቅቦ ብቻ) የፀደቀው ይህ አዲስ ደንብ፤ በርካታ አንኳር እና አዳዲስ አሰራሮችን አስተዋውቋል። ማንኛውም የስራ አስፈፃሚ አባል በአንድ የ4 ዓመት የምርጫ ዘመን የሚያገለግል ሲሆን፣ ከሁለት የምርጫ ዙር በላይ በስልጣን መቆየት እንደማይችል ተወስኗል። በስራ አስፈፃሚው ስብስብ ውስጥ የግድ ቢያንስ አንድ የቀድሞ አትሌት፣ አሰልጣኝ ወይም የስፖርት ሳይንስ ባለሙያ መካተት እንዳለበት ደንቡ የሚያስገድድ ሲሆን የውጭ አትሌቶች ቅጥርን በተመለከተም  የሀገር ውስጥ የአትሌቲክስ ክለቦች የውጭ ሀገር አትሌቶችን በክለባቸው መቅጠር የሚችሉበት አዲስ ዕድል ተከፍቶላቸዋል። ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ጋር በተያያዘ ደግሞ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚነት ምርጫ ላይ መወዳደር እንደማይችሉ በደንቡ በግልፅ ተቀምጧል። አህጉራዊ የአትሌቲክስ ተቋማትም በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተገኝተው ድምፅ የመስጠት መብት አግኝተዋል። ከመተዳደሪያ ደንቡ ማሻሻያ በተጨማሪም፤ ጉባኤው የፌዴሬሽኑን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እና ሌሎች ተያያዥ ሰነዶችን  መርምሮ ውሳኔ አሳልፎባቸዋል።

✍️ ዮናታን አየለ

Leave a Reply

Your email address will not be published.