አንጋፋው እና ተወዳጁ የስፖርት ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አረፈ

ዜና እረፍት!

አንጋፋው እና ተወዳጁ የስፖርት ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ

በሁሉም የስፖርት አይነቶች፣ በሁለቱም ፆታዎች እና በሁሉም የእድሜ እርከን ውድድሮች ላይ
የታዳጊዎች፣ የሴቶች፣ የጤና ቡድኖች፣ አንደኛ ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ፣ ፕሪምየር ሊግና የመታሰቢያ ውድድሮች ላይ ሳይቀር በመገኘት ለስፖርት ቤተሰቡ የተለያዩ መረጃዎችን ላለፉት 30 ዓመታት ሲያደርስ የቆየው አንጋፋውና ታታሪው የስፖርት ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በድንገት ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል።
ጋዜጠኛ መሸሻ በተለይም በህትመት ውጤቶች ላይ በሚያቀርባቸው ፅሁፎች ታዋቂና ታማኝ ምንጭ የነበረ ሲሆን በካምቦሎጆ፣ ሊግ ስፖርት፣ ሀትሪክ ፣በሻምፒዮን፣ ማራቶን፣ ግሎባል፣ ይድነቃቸው፣ ካታናንጋ፣ አዲስ ስፖርት፣ ስፖርት (መፅሔት ጭምር) ጋዜጦች እና በቤስት ስፖርት መፅሔት እንዲሁም በኤፍ ኤም 90.7 (ዛሚ) እና 96.3 የራዲዮ ፕሮግራሞች ላይ በመስራት ተወዳጅነት እና ከበሬታ ያተረፈ ተወዳጅና ታማኝ ጋዜጠኛ ነበር።

በኢትዮጵያ ስፖርት ትልቅ አሻራ ያስቀመጠው መሸሻ ወልዴ የቀብር ስነ-ስርዓትም ነገ 5 ሰዓት በቀጨኔ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን እንደሚፈፀም ታውቋል።

ኢትዮጵያን ስፖርት በአንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.