የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ በዛሬው እለት በፌዴሬሽኑ መሰብሰብያ አዳራሽ በድሬዳዋ ከተማ በሁለት ዙር የተካሄዱትን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች አስመልክቶ ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሸረፋ ደሌቾ ፣ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ልኡልሰገድ በጋሻው ፣ የዳኞች ልማት እና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሲያምረኝ ዳኜ እና የኮሚቴ አባላት የተገኙ ሲሆን አቶ ሸረፋ በውድድሩ ወቅት የነበሩትን ሂደቶች ከመወዳደሪያ ሜዳ አንፃር ፣ የቡድን አመራሮችን ፣ የፀጥታ ሁኔታን ፣ የጨዋታ አመራሮች እና ኮሚሽነሮችን ነባራዊ ሁኔታዎች ታሳቢ በማድረግ መወያየታቸውን በዚህም የሜዳው በተወሰኑ ጨዋታዎች ወቅት ጭቃ ማስቸገሩን እና ያንንም በማስተካከል ጨዋታዎች እንዲካሄዱ መደረጋቸውን፣ በርከት ያሉ የቡድን አመራሮች ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎትን የማቅረብ ሁኔታ እንደነበርና በዚህም ጥሩ ግንኙነቶች እንደነበሩ እንዲሁም የጨዋታ አመራሮችን በተመለከተ ከተወሰኑ አመራሮች በስተቀር አብዛኛው በሚባል መልኩ የተሻለ የጨዋታ ህግና ደንቡን መሠረት በማድረግ ሥርዓትን በተከተለ መልኩ ሲመሩ የቆዩ እንደነበርና ጥቂት የጨዋታ አመራር የቴክኒካልና አስተዳዳራዊ ስህተቶችን በመፈፀማቸው ተገቢውን የማስተካከያ ቅጣት የመስጠት ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል፡፡
አክለውም ኮሚሽነሮችን በተመለተ የሪፖርት አሞላል ሂደቶቹን በሚመለከቱበት ወቅት በርካቶቹ የተሻለ ሥራ የሰሩ እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶች ላይ ችግሮች መመልከታቸውን ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም ክለቦችን በተመለከተ አብካኞች ጥሩ ሥነምግባርን በተላበሰ መልኩ ውድድሩን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን እና 2 እና 3 የሚሆኑት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት አላስፈላጊ ሁኔታዎችን ሲያከናውኑ ያስተዋሉ መሆናኑን አስረድተዋል፡፡ ፀጥታን በተመለከተም ውድድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስተማማኝ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ቀጣይ ሥራዎችን በተሻለ ለመሰራት ኮሚቴው አቅጣጫ በመያዝ በአዳማ የሚከናወኑ የኘሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ታሳቢ በማድረግ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲያስችል “እነማን ጨዋታዎችን ማጫወት ይገባቸዋል” በማለት ዳኞችን በጥራት የመመልመልና የማዘጋጀት ሥራ በመስራት 30 ዋና እና 33 ረዳት ዳኞች በአጠቃላይ 63 ዳኞችን በብቃት የመመልመል ሥራ መሠራቱን እንዲሁም ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ የአቅም ግምባታ ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሸረፋ አስረድተዋል፡፡