በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ መዳረሻን ይጠቁማል የተባለለት የኤቲሀዱ ጨዋታ።
▪️ሁለቱም ቡድኖች የዘንድሮው የውድድር ዘመን ሊጠናቀቅ 7 ጨዋታዎች ብቻ እየቀሩት በመካከላቸው ያለው የነጥብ ልዩነት 1 ብቻ ሆኖ የተገናኙበት መርሀ-ግብር ነው። ማንቸስተር ሲቲ በአሰላለፉ ላይ ከጥር በኋላ ቋሚ ሆኖ ለቡድኑ ተጫውቶ የማያውቀውን ጋብሬል ጄሱስን የአጥቂ መስመሩን እንዲመራ ፔፕ ጋርዲዮላ አደራ ሰጥተውት ወደ-ሜዳ አስገብተውታል።
▪️ሊቨርፑሎች በበኩላቸው የፊት መስመራቸው እንዴት ይሆናል የሚለው ጥያቄ ዲዬጎ ጆታን በማስገባት የመለሱ ሲሆን በግራ እና በቀኝ የተለመዱት ሳድዮ ማኔ እና ሞሀመድ ሳላይ ያጣምሩታል።
▪️ጨዋታው በተጀመረ ገና 5 ደቂቃ ሳይሞላ ስተርሊንግ ያገኘውን ግልጽ የማግባት እድል መጠቀም አልቻለም። ወዲያውኑ የ30 አመቱ ድንቅ ቤልጂየማዊ ኬቨን ዴብራይን ከ20 ሜትር ርቀት ላይ አክርሮ የመታው ኳስ ጆኤል ማቲፕን እግርን ገጭታ የአሊሰን ቤከር መረብ ላይ አረፈች።
▪️ከ7 ደቂቃ ቀኋላ ሊቨርፑል በአስደናቂ የቡድን እንቅስቃሴ ከትሬንት አርኖልድ የመጣውን ፖርቹጋላዊው ኳስ ዲዬጎ ጆታ በሚገባ በመጠቀም ቡድኑን አቻ አድርጓል።
▪️ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላ በአንፃራዊነት የጨዋታው ፍሰት ቀዝቀዝ ያለ ሲሆን ማንቸስተር ሲቲ አልፎ-አልፎ ኢላማቸውን የጠበቁ ባይሆኑም አስደንጋጭ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል።
▪️በ36ኛው ደቂቃ ከጆአዎ ካንሴሎ የተሻገረለትን ኳስ ጋብሬል ጄሱስ በማስቆጠር ሲቲን በጨዋታው እንደገና መሪ ማድረግ ቻለ። ጄሱስ ያስቆጠራት ይህች ግብ በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ግብ ስትሆን ከ117 ቀን በኋላም የተገኘች ሆናለች።
▪️የመጀመሪያው አጋማሽ በማንቸስተር ሲቲ 2-1 መሪነት ተጠናቋል። ሊቨርፑል በዚህ የውድድር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ እየተመራ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።
▪️ከእረፍት መልስ ገና 1 ደቂቃ ሳይሞላው በ46ኛ ሰከንድ ከሞ ሳላህ የተሻገረለትን ኳስ ሳድዮ ማኔ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ማንቸስተር ሲቲን በገጠመባቸው ጨዋታዎች 8ኛ ጎሉ ሆና በልደቱ ቀን ተመዝግባለች።
▪️በ62ኛው ደቂቃ ማንቸስተር ሲቲ ጨዋታውን ለ3ኛ ጊዜ መምራት የቻለበትን እድል በስተርሊንግ አማካኝነት ቢያገኝም በቪ.ኤ.አር ከጨዋታው ውጪ ተብሎ ተሽሯል። ከዚ እንቅስቃሴ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄን መሰረት ያደረገ ጨዋታ ለመተግበር ጥረት ያደረጉ ሲሆን ኳስን በማንሸራሸር እና የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር በማስከፈት የጨዋታው መሪ ለመሆን ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ማህሬዝ ያገኘውን እድል መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። አስደናቂ የነበረው ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ከ 2018 በኋላ ሊቨርፑል ኤቲሀድ ላይ ማሸነፍ አልቻለም። ቢሆንም ግን ማንቸስተር ሲቲን እግር በእግር በመከተል ዘንድሮም ተፎካካሪ መሆናቸውን አሳይተውበታል። ሲቲዎች ከቀሩት 7 ጨዋታዎች 21 ነጥብ በማሳካት አፍንጫቸው ስር ለሚገኙት ሊቨርፑሎች ምንም አይነት እድል ላለመስጠት እንደሚሞክሩ አያጠያይቅም። የውድድር ዘመኑ ሊጠናቀቅ 7 ጨዋታዎች እየቀሩ ማንቸስተር ሲቲ 74 ነጥብ ሊቨርፑል በ73 ነጥብ ይከተላል።
ሚካኤል ደጀኔ።