ግዙፋ የባሕር ዳር ስታዲየም በካፍ ታገደ።
የባሕር ዳር ስታዲየም በካፍ መታገዱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ
የብሔራዊ ቡድን ውድድሮችን ላለፉት ዓመታት ሲያስተናግድ የቆየው የባህር ዳር ብሔራዊ ስታዲየም የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን እና የአፍሪካ የክለብ ሻንፒዮና ውድድሮች እንዳይካሄድበት ማገዱን ካፍ አሳወቀ።
የባህር ዳር ብሔራዊ ስታዲየም የካፍ የስታዲየም መመዘኛ መስፈርቶችን ሙሉ በሙሉ ባለማሟላቱ በገደብ ውድድሮችን እዲያስተናግድ መደረጉ ይታወሳል።
ሰሞኑን የካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ ማኔጀር መሐመድ ሲዳት ኢትዮጵያ በመምጣት የተለያዩ ስታዲየሞችን የገመገሙ ሲሆን ፤ በዋንኛነት የባሕር ዳር ስታዲየምን ገምግመው ለተመሳሳይ የስታዲየም ምልከታ ወደ ኬንያ ማቅናታቸው ይታወሳል።
የተለያዩ የብሔራዊ ቡድን ውድድሮችን ሲያስተናግድ የቆየው የባህር ዳር ስታዲየም ከዚህ በኋላ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን እና የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን እና ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮችን እንዳይካሄድበት ማገዱን ካፍ በትናንትናው እለት ጥቅምት 7/2014ዓ.ም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።
በደብዳቤውም ከኦክቶበር 20 በፊት ኢትዮጵያ በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና ጋር የምታደርገውን ጨዋታ በማን ሀገር በየትኛው ስታዲየም ለመጫወት እንደምትመርጥ ለካፍ በአስቸኳይ እንድታሳውቅ ካፍ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ይህ ሳይሆን ቢቀር ካፍ ጨዋታውን ወደ ተጋጣሚዋ ሀገር እንደሚወስድ አሳውቋል።
ካፍ በደብዳቤው ባህር ዳር ብሔራዊ ስታዲየም ከዚህ በታች የተገለጹትን መስፈርቶች ባለማሟላቱ የታገደ መሆኑን ገልጿል።
1. የጨዋታ ሜዳው እና ለጨዋታ ሜዳው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ባለማማላቱ፤ በተለይ የመጫወቻ ሳሩ ደረጃውን የጠበቀ አለመሆኑ፣ የምሽት ጨዋታዎችን ለማካሄድ መብራት ያልተገጠመለት መሆኑ፣ ፕሮፌሽናል የጫወቻ ሜዳ አስተዳደር በተለይ ሳሩን የሚከታተል ካምፓኒ አለመኖር፣ የተተከለው የሳር ጥራት ደረጃውን ያልጠበቀ መሆኑ ( ሳሩ በሌላ ደረጃውን በጠበቀ የተፈጥሮ ሳር ሙሉ በሙሉ መቀየር ያለበት መሆኑ)፣ ተቀያሪ ተጫዋቾች ሚቀመጡበት ወንበር ደረጃውን ያልጠበቀ መሆኑ።
2. የቡድኖች እና የጨዋታ አመራሮች ማረፊያ
መልበሻ ክፍሎች ደረጃቸውን ያሟሉ አለመሆን፤ መልበሻ ክፍሎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ መቀመጫዎች ያስፈልጓቸዋል። በመልበሻ ክፍሎች የሚገኙ መታጠቢያ ክፍሎች ብዛት በስታንዳርዱ የተቀመጠው ቁጥር ሊኖር ይገባል፤ በመልበሻ ክፍሉ የሚገኙ ማሟቂያ ቦታዎች አርቴፊሻል ተርፍ ሊነጠፍባቸው እና የዳኞች ማረፊያ ክፍሎች ደረጃቸውን ያሟሉ ሊሆን ይገባል ብሏል።
3. የህክምና ክፍል
የህክምና ክፍሉ ማቴሪያሎችን ሊያሟላ ይገባል። ለምሳሌ አውቶማቲክ ቬንትሌተር፣ ቀላል ቀዶ ጥገና መስሪያ መሳሪያዎች፣ ካርዲያክ ሞኒተር፣ ስታንዳርዱን የጠበቀ ዶፒንግ መቆጣጣሪያ ክፍል አለመኖር ወዘተ…
4. ተመልካቾች ፋሲሊቲን በተመለከተ
የተመልካቾች መቀመጫ አለመኖር፣በስታዲየሙ ለተመልካቾች የሚያገለግል የካፍቴሪያ ፋሲሊቲ ወለመኖር፣ ስታዲየም የእሳት አደጋ መከላከያ እና የደህንነት ብቃት የሚገልጽ ሰርተፍኬት ያለው አለመሆን፣ ስታዲየሙን ለመቆጣጠር የሚያገለግለው ክፍል በተለየ ቦታ መቀመጡ፣
5. VIP እና የመስተንግዶ ማቅረቢያ አካባቢ
ደረጃቸውን የጠበቁ ለክብር እንግዶች የሚሆኑ ቋሚ ከወለሉ ጋር የታሰሩ ወንበሮች አለመኖር፣ የክብር እንግዶች የሚገኙበት ቦታ WiFi ፣ቴሌቪዥን እና ሳውንድ ሲስተም ያሌለ መሆኑ፤ የክብር እንግዶች የሚገኙበት ቦታ በመስታውት የተለየ አለመሆኑ፣ ለክብር እንግዶች የሚሆን ላውንጅ ያለው አለመሆኑ፣ የVIP እና የሚዲያ መወጣጫው አንድ ላይ መሆን፣ ለVIP በግልጽ የተለየ የመኪና ማቆሚያ አለመኖር
6. ሚዲያን በተመለከተ
በስታዲየሙ ደረጃውን የጠበቀ የሚዲያ ማእከል አለመኖር፣ ፎቶ አንሺዎች በሚቀመጡበት የጎል ጀርባ የኢንተርኔት ኮኔክሽን፣ መብራት ማከፋፈያ እና ወንበር አለመኖር ፣ ደረጃውን ያሟላ ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አለመኖር
7. የልምምድ ሜዳዎች
የልምምድ ሜዳዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆን፣ በምሽት ልምምድ ሊያሰራ የሚችል መብራት የሌላቸው መሆን፣ ተቀያሪ ተጫዋቾች መቀመጫ ወንበር እና መልበሻ ክፍሎች የሌላቸው መሆን፣ ሻወር እና መጸዳጃ ቤት አለመኖር ወዘተ…
ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች የባህር ዳር ብሔራዊ ስታዲየም ለመታገዱ ምክንያት ሆነዋል።
መሀመድ ሲዳት በኢትዮጵያ በነበራቸው አጭር የምልከታ ጊዜ ከባህር ዳር ስታዲየም በተጨማሪ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም እና የጅማ ዩንቨርስቲ ስታዲየምን ተመልክተዋል።
በምልከታቸው ወቅት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከመስፈርቱ አንጻር በርካታ መሟላት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ በመግለጽ ስታዲየም ለወደፊት የተጓደሉትን ነገሮች ካሟላ ወደ ፊት የገምጋሚ ቡድን እንደሚልኩ የገለጹት የካፍ ክለብ ላይሰንሲግ ይህ እስካልሆነ ድረስ አሁን ባለው ሁኔታ ምንም የኢንተርናሽናል ውድድር ማስተናገድ እንደማይችል አሳውቀዋል።
በአንጻሩ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም በእድሜ ደረጃ ሚዘጋጁ ውድድሮችን እና የሴት የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን በጊዚያዊነት ማስተናገድ እንደሚችል የገለጹ ሲሆን ፤ ማረጋገጫ ደብዳቤውንም በአጭር ቀናት ውስጥ እደሚልኩ የገለጹ ሲሆን፤ የሐዋሳ ዩንቨርስቲ ስታዲየምን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በኢ.እ.ፌ ክለብ ላይሰንሲግ የተገመገመ እና ሪፖርቱ የደረደሳቸው መሀመድ ሲዳት መጫወቻ ሳሩ ደረጃውን ያልጠበቀ፣ ሜዳው አጠገብ ያለው መሮጫ መም በምርጫ መም እንዲሰፍን ወይም በሳር ሙሉ በሙሉ እንዲሸፈን ከዚህ ቀደም የገለጹ ሲሆን መልበሻ ክፍሎቹ በአዲስ መልክ ሊሻሻሉ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
መረጃው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው