የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ጋር የሁለትዮሽ የስራ ስምምነትን እና ትስስር ሰነድ ተፈራረመ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ጋር በከተማዋ ሁለንተናዊ የስፖርት ዕድገት እና ለውጥ ዙሪያ በጋራ ለመስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ትናንት የካቲት 11 በካፒታል ሆቴል የሁለትዮሽ የፊርማ ስነ-ስርዐት አካሂደዋል ።
በመድረኩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በላይ ደጀን ከተማችን አዲስ አበባ ስሟንና ተግባሯን የሚመጥን የስፖርት ልማትና ተሳትፎዎች እያደረገችና ይህንንም አስቀጥላ የምትሄድ በመሆኑ ለዚህ ተግባር ወደ ማህበረሰቡና የስፖርት ቤተሰቡ ጋር ለመድረስ የመገናኛ ብዙሃን በተለይ የስፖርት ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች ወሳኝ ናቸው ብለዋል ።ኮሚሽነር በላይ አያይዘውም የስፖርት ጋዜጠኞች በነፃነት በዕውቀትና ሙያ ተክነው ግልፅ ፣ ሚዛናዊና እውነተኛ ዘገባ ለማድረስና የሚታዩ ክፍቶችን በማሳየት እርምት እንዲወሰድ በማድረግ የማይተካ ሚና ስላላቸው አቅማቸው በስልጠና ሊዳብር ይገባል ለዚህም ኮሚሽኑ ድጋፉንና ዕገዛውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።
የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ነዋይ ይመር ጋዜጠኝነት ሙያችን ሀገርንና ህዝብን ማገልገል ግዴታችን በመሆኑ በገባነው የውል ስምምነት መሠረት እንሰራለን ብሏል ።
ለ45 ቀናት የሚቆይ የአቅም መገንቢያ ስልጠና ዕድሜያቸው ከ28 ዐመት በታች ለሆኑ ወጣት የስፖርት ጋዜጠኝነት ፍቅርና ልምድ ላላቸው ከየካቲት 22/2013 ዓ,ም, ጀምሮ በሚወጡ የስልጠና መርሀ ግብር ጊዜና ቦታ እንደሚሰጥ ለዚህም ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ተገልፆል ።
የሁለትዮሽ የአጋር የስራ ስምምነትን እና ትስስር ሰነድን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በላይ ደጀን ከኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕረዚዳንት ከጋዜጠኛ ነዋይ ይመር ጋር ተፈራርመዋል ።