እስካሁን ዕልባት ያላገኘዉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የስልጠና ማንዋል ዕልባት ሊያገኝ ነዉ፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከተመሠረተ 77ኛ ዓመቱን ቢደፍንም እስከአሁን የሀገሪቱ እግር ኳስ የሚመራበት የራሱ ማንዋል የለውም፤ይሄንን ተከትሎ 12 ኢንስትራክተሮችን ያቀፈ የባለሞያዎች ቡድን የሀገሪቱ የስልጠና ማንዋል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚዘጋጅበት ዙርያ በዛሬው ዕለት በፌዴሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲመክር አርፍዷል።

በቀጣይ የሀገሪቱ እግር ኳስ ይመራበታል ተብሎ በታመነበት የስልጠና ማንዋሉን በማዘጋጀቱ ሂደት ላይ ወደ አሜሪካን ሄደው ኑሮአቸውን ካደረጉት ከዶ/ር ጌታቸው በስተቀር ሀገሪቷ ያልዋት 12ቱም የካፍ ኢንስትራክተሮች ተሳታፊ ሆነውበታል።
እንደ ዜና ምንጮቻችን ከሆነ 12ቱም የካፍ ኢንስትራክተሮች ተሳታፊ የሆኑበት የስልጠና ማንዋል ዝግጅት በአራት ምድብ ማለትም በD፣በC፣በB እና በA ላይሰንስ ተከፍለው ውይይት አድርገዋል፤ 12ቱ ኢንስትራክተሮች ሲያደርጉት በነበረው ጥናት ዙሪያ ውይይት የተደረገ ሲሆን ማንዋሉን ለማጠናቀቅ የሚረዳ ለመጨረሻ የሚሆን ግብአትም ከውይይቱ መገኘቱ ታውቋል።
ሶስት ሶስት ኢንስትራክተሮች በአራቱም ግሩፖች ተደልድለው ሲያደርጓቸው የነበሩት ውይይቶች በቀጣይ የሀገሪቱ እግር ኳስ ከዘልማድና ከተዘበራረቀ አሠራር ተላቆ ወጥነት ባለው የስልጠና መንገድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ይመራበታል የሚል ዕምነትም ተጥሎበት ነው የማንዋል ዝግጅት እየተደረገ ያለው።

በዚህም መሠረት የስልጠና ማንዋሉ በካፍ ዕውቅና ያለውና በካፍ የስልጠና ማንዋል መሠረት ተቃኝቶ የሚዘጋጅ ሲሆን በቀጣይ ሁለትና ሶስት ወራትም ውይይቱና ጥናቱ ሲጠናቀቅ የ77 ዓመት አዛውንት የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመራበት የራሱ የስልጠና ማንዋል ባለቤት እንዲሆንም ያደርገዋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.