የራስ አል ካይማ ግማሽ ማራቶን በመጭው የካቲት ወር አጋማሽ እንደሚደረግ ታወቀ
በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች አል ማርጃን ደሴት የሚካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር ከመላው ዓለም የተውጣጡ የርቀቱ ኮከብ አትሌቶችን ለመቀበል ዝግጅቱን እያጠናቀቀ እንደሚገኝ እና በመጭው የካቲት ወር አጋማሽ እንደሚደረግ ገልፍ ቱዴይ ዘግቧል።
የ21ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ይህ ውድድር ባለፈው አመት ሲካሔድ ከአምስት ሺ ሁለት መቶ በላይ አትሌቶችና ተሳታፊዎች የተካፈሉ ሲሆን በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አባብል የሻነህ ርቀቱን በ 64፡31 ሰዓት በማጠናቀቅ የሴቶችን ብቻ የዓለም ክብረወሰን በሃያ ሰከንድ ማሻሻሏ ይታወሳል።
‹‹የዘንድሮውን ውድድር ይፋ በማድረጋችን እጅግ ተደስተናል፣ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የርቀቱን የሴቶች ብቻ የዓለም ክብረወሰን በሃያ ሰከንድ በማሻሻል አስደናቂ ውጤት በውድድሩ ማስመዝገብ እንደሚቻል አሳይታለች፣ ይህ የዓለም ክብረወሰን በቅርቡ በዓለም አትሌቲክስ እውቅና እንደሚያገኝ ተስፋ እያደረግን በዘንድሮው ዓመትም የተዋጣለት ውድድር ለማድረግ እየተዘጋጀን ነው፣ የራስ አል ካይማ ግማሽ ማራቶን ውድድር በዓለማችን በርቀቱ ፈጣን ሰዓት የሚመዘገብበት ውድድር እንዲሆንም ጠንክረን እንሰራለን› በማለት አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
የረጅም ርቀት አትሌቶች ባሉት ውስን ቦታዎች ከወዲሁ መመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው የተገለፀ ሲሆን ምዝገባው በኤሌክትሮኒክስ መንገድ የሚከናወን ይሆናል።